SHARE

ኢትዮ-ቴሌኮም በሚሰጠው አገልግሎት በዓለም አቀፍ ደረጃ የአልማዝ ተሸላሚ መሆኑን ገልጧል።

ድርጅቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው ሽልማቱን ያገኝው እየተጠናቀቀ ባለው የፈረንጆች 2017 ዓመት ለማሕበረሰቡ የኢኮኖሚ እድገት ባበረከተው ሚና እና በሰጠው ጥራት ያለው አገልግሎት ተሸላሚ ሆኗል።

ሽልማቱን ያዘጋጀው መቀመጫውን ስዊዘርላንድ ያደረገው ‹የአውሮፓ የጥራትና ምርምር ማሕበረሰብ› የተሰኝ ዓለም አቀፋዊ ተቋም መሆኑን አስታውቋል።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር አንዱዓለም አድማሴ በኦሰትሪያ ቬና ከተማ ከአምስት ቀናት በፊት ሽልማቱን ተቀብለዋል።

ድርጅቱ ለማሕበረሰቡ ኢኮኖሚ እድገት የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡና የተሻለ የማደግ ጥረት እና ልሕቀት ላላቸው ተቋማት እውቅና የሚሰጥ መሆኑ ነው የተገለፀው።

የሽልማቱ አሸናፊ ተቋማት ምርጫ የተደረገው በደንበኞች አስተያየትና የገበያ ጥናት ከተጠቃሚዎች በተገኝ መረጃ እንዲሁም ይህንን ሽልማት ከዚህ በፊት ከወሰዱ ተቋማት የሚሰበሰቡ ውጤቶችን መሰረት ያደረገ ነው።

በዚህ ዓመት ከአውሮፓ፣ ከእስያ ፣ ከአሜሪካ ፣ ከአፍሪካና ከአውስትራሊያ ውጤታማ የስራ አፈጻጸም ካሳዩና የሽልማቱ አሸናፊ ከሆኑ ተቋማት መካከል የኔዘርላንዱን ፊሊፕስና የጀርመኑ ቢኤምደብሊው ኩባንያዎች ይገኙበታል።

ከዚህ በተጨማሪም ሌሎች 69 ስመጥር ተቋማትና ግለሰቦች ሽልማቱን የተቀበሉ ሲሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድም በሽልማቱ መካተቱ አመልክቷል።